NA Hadiya Diaspora in Position Paper

የሀዲያ ብሔራዊ ክልል ጥያቄን በተመለከተ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የሀዲያ ተወላጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የሀዲያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 እና 47 በሚደነግገው መሰረት ሀዲያ በክልልነት እንዲደረጅ ለረጅም አመታት በተደጋጋሚ የተጠየቀውን መሰረት በማድረግ የሀድያ ዞን ምክር ቤት በህዳር ወር 2011 ዓ/ም ባካሄደው አራተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ሀዲያ በክልልነት እንዲደረጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ የሀዲያ ዞን መስተዳድር ጽ/ቤትም ሀዲያ በክልልነት እንዲደረጅ በሀዲያ ዞን ምክር ቤት በተወሰነው ውሳኔ ላይ የደቡብ ክልል መስተዳድር ጽ/ቤት ሕዝባ ውሳኔ እንድያስፈጽም ወደ ደቡብ ክልል ምክር ቤት መላኩ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን እስከአሁን ከደቡብ ክልል መንግስት ምንም አይነት ምላሽ አልተሰጠም፡፡

ሰሞኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክሪያሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሀዲያን ጨምሮ የደቡብ ብሔሮች በክልልነት ለመደራጀት ያቀረቡትን ሕገ፡መንግስታዊ ጥያቄዎች ወደ ጎን በመተው በህግ ከተሰጠቸው ስልጣን ውጪ ሕገ ወጥ የሆነ አስተዳደራዊ የክልል አወቃቀር ውሰኔ ለመስጠት ስብሰባ መቀመጣቸው እየተነገረ ነው፡፡

አንድ መረሳት የሌለበትን ታሪካዊ እዉነታ ልናስታዉሳችሁ እንወዳለን። የሀዲያ ህዝብ የራሱን ዕድል ራሱ ለመወሰንና ለዴሞክሪሲ በታሪኩ ዉስጥ ያደረጋቸዉን ተጋድሎዎች ማስታወስ ይጠቅማል። ዛሬ ለፋሽን የጀመረዉ አይደለም። የጥንቱን ታሪክ በዚህ ጽሁፋችን መዘርዘር አንሻም። ነገር ግን በ1992 ምርጫ ጊዜ በትግል ኣምባ የረገፉትን የሀዲያ ሰማዕታት ለኣብነት እናስታዉችኋለን።

እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የሀዲያ ተወላጆች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለተን በመሆኑ አቋማችንን እንደሚከተለው እንገልጻለን፡፡

1. የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ያጸደቀውን ሀዲያ በብሔራዊ ክልልነት የመደራጀት ሕገ መንግስታዊ ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ሕገ ወጥ የሆነ አስተዳደራዊ የክልል አወቃቀር ውሰኔ መስጠት እንደማይችል በአጽንዖት እናሳውቃለን፡፡

2. የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ያጸደቀውን ሀዲያ በብሔራዊ ክልልነት የመደራጀት ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው የሀዲያ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በሕግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የሚወስነው ማንኛውም የክልል አደረጃጃት ውሳኔ ህጋዊ መሰረት የሌለው ስለሆነ በሀዲያ ሕዝብ ዘንድ ምንም አይነት ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴም ይሁን ማንኛውም ባላስልጣን ህገ መንግስቱን የሚፃረር ውሳኔ ቢወስን የሀዲያ ሕዝብ በኢትዮጲያና በአለም አቀፍ ሕጎች ለመብቱ ይከራከራል እንጅ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ውሳኔ በጭራሽ አይቀበልም፡፡

3. እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የሀዲያ ተወላጆች በሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት የጸደቀውን ውሳኔ ማጽደቅም ይሁን መቀየር የሚቻለው በሀዲያ ሕዝብ በሚደረግ ሪፌረንደም ብቻ መሆኑን አጥብቀን ልናሳውቅ እንፈልጋለን፡፡

ስለዚህ እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር የሀዲያ ተወላጆች የሀዲያ ሕዝብ በክልልነት ለመደራጀት ያቀረበውን ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሀድያ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የጸደቀው ውሳኔ እንዲከበርና የደቡብ ክልልና የፌዴራል መንግስት በሕገ መንግስቱ በግልጽ በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት ሕዝባ ውሳኔ እንዲያስፈጽም አጥብቀን እየጠየቅን የሀዲያ ብሔርን በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የሚጻረር ማንኛውንም ሕገ ወጥ እርምጃ አጥብቀን እንቃወመለን፡፡

ህገመንግስቱ ይከበር!

ከከሀዲያ ሰፊ ሕዝብ ውጪ የሀዲያን እድል ማንም አይወስንም!

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

6 thoughts on “የሀዲያ ብሔራዊ ክልል ጥያቄን በተመለከተ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ የሀዲያ ተወላጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ”

%d bloggers like this: