Hadiya Kabeera Youth Demonstration for Rights

ሀዲያ ዞን ምክር ቤት የሀዲያን ክልል ለማቋቋም በሙሉ ድምጽ የወሰነበትን ታሪካዊ ውሳኔ አንደኛ አመት አስመልክቶ የአለም አቀፍ የሀዲያ ዲያስፖራ ህብረት ያስተላለፈው የአቋም መግለጫ

የሀዲያ ህዝብ ለብዙ መቶዎች አመታት ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ ከሌሎች ህዝቦችና አገሮች ጋር ግንኙነቶችን ሲያደርግ የኖረ፣ በባህሉና ቋንቋው ኩሩ የሆነ ህዝብ ነው።

ነገር ግን የሀዲያ ህዝብ በታሪክ አጋጣሚ በሀይል ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተነጥቆ ቆይቷል። ቋንቋ፣ ሀይማኖትና ባህሉን እንዲተውም ከባድ ጫና ተደርጎበት ለዛሬ ደርሷል። እነዚህን መብቶች መልሶ ለመጠቀምም በተለያዩ ጊዜዎች ጦርነቶችና ሰላማዊ ትግሎችን አድርጓል።

አሁን ያለንበት ዘመን ጥያቄዎች በሰላማዊና ዲሞክረሲያዊ መንገድ ተጠይቀው በዚሁ መንገድ መመለስ ያለባቸው መሆኑን በጽኑ እናምናለን።

በዚህ መሰረት የሀዲያ ህዝብ በህገ መንግስቱ የተረጋገጠለትን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በመጠቀም የሀዲያን ክልል ለመመስረት በተወካዮቹ አማካኝነት በሙሉ ድምጽ ከወሰነ አንድ አመት ሞልቶታል።

ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ለክልሉ ምክር ቤት ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለህዝበ ውሳኔ እንዲቀርብ ህገ መንግስቱ በአንቀጽ 47 (3/ ለ) ቢደነግግም ይህ ሳይደረግ ቆይቷል።

ጥያቄውን በዲሞክረሲያዊ ሁኔታ መመለስ የክልሉ መንግስት ግዴታ ቢሆንም ይህን ግዴታ ከመወጣት ይልቅ ሂደቱን ለማደናቀፍ ጉዳዩ በጥናት ይመለስ የሚል ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ መርጧል። በሀዲያ ዞን የተከሰተ ወይም የጸጥታ ስጋት የፈጠረ ክስተት በሌለበት ሁኔታም ዞኑ በኮማንድ ፖስት ስር ተደርጎ መሰረታዊ ነጻነቶችና መብቶች ታግደዋል።

ይህ አካሄድ የሀዲያን ህዝብ መብት የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር የህግ የበላይነትን የሚጻረር፤ በህግና በመንግስት ላይ አመኔታ የሚያሳጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሚያደርግ መሆኑ ግልጽ ነው።

በመሆኑም የሀዲያ ዲያስፖራ ህብረት በሰፊው ከመከረበት በኋላ የሚከተለውን አቋም መግለጫ አውጥቷል።

1. በደኢህዴን የቀረቡት ሶስቱም አማራጮች የሀዲያ ህዝብ የጠየቀውን የመብት ጥያቄ የማይመልሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ ህገ መንግስቱን የሚጻረሩ በመሆናቸው የማንቀበላቸው መሆኑን፤

2. የሀዲያ ዞን ምክር ቤት የወሰነውን የክልልነት ጥያቄ የደ/ብ/ብ ክልል ምክር ቤት በአስቸኳይ ለህዝበ ውሳኔ እንዲመራ፤

3. በሀዲያ ዞን የታወጀው የኮማንድ ፖስት አዋጅ አላስፈላጊና ህገ መንግስቱን ያላከበረ ስለሆነና ህዝቡ መብቱን እንዳይጠቀም የሚያደርግ አፋኝ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲነሳ፤

4. ኮማንድ ፖስት መታወጁን ምክንያት በማድረግ በዞኑ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት የመብት ጥሰቶች እንዲቆሙ፤

5. የፌደራልና የደቡብ ክልል ህገ መንግስቶችን በመጣስ የሀዲያ ህዝብ መብት እንዳይጠበቅ የሚያደርጉ ማንኛውም አካላት ለህግ እንዲቀርቡ፤

6. የሀዲያን ህዝብ እኩልነት፣ ከሉዐላዊነቱ የመነጨውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚሸረሽርና የሚጥስን ስርዐት አጥብቀን እንደምንቃወምና እንደምንታገል እንገልፃለን፤

7. የክልልነት ጥያቄውን በቀጥታ ወደ ህዝበ ውሳኔ ባለመውሰድ ማዘግየት ኢ-ህገመንገስታዊ መሆኑንና በሌላ አኳኋን ጥያቄውን ማስኬድ ከህገ መንግስቱ ውጪ በመሆኑ የሀዲያ ዞን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በአንድ አመት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ካልተደረገ በታህሳስ 17/ 2012 ዓ/ም የሀዲያ ብሔራዊ ክልል የሚታወጅ መሆኑን እናሳውቃለን።

Hadiya National Flag
Hadiya National Flag

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

5 thoughts on “ሀዲያ ዞን ምክር ቤት የሀዲያን ክልል ለማቋቋም በሙሉ ድምጽ የወሰነበትን ታሪካዊ ውሳኔ አንደኛ አመት አስመልክቶ የአለም አቀፍ የሀዲያ ዲያስፖራ ህብረት ያስተላለፈው የአቋም መግለጫ”

%d bloggers like this: