Hadiya Ethiopia Elders Assembly

በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በኢሲያና በሌሎችም የአለም ዙሪያ ከሚገኙ የሀዲያ ተወላጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የሀዲያ ብሔር በመካከለኛው ኢትዮጵያ ጠንካራ የሀዲያ ስርወ መንግስት መስርቶ ለብዙ መቶዎች አመታት ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር የኖረ፣ የራሱ ግዛት የነበረው፣ የዜይላ ወደብ ፌዴሬሽን አባል የነበረና የታወቀ የውጪ ንግድ ግንኙነት የነበረው፣ በማንነቱ፣ በባህሉና በቋንቋው ኩሩ የሆነ ብሔር ነው። ሀዲያ የዳበረ የአስተዳዳር ስርአትና ባህል ያለው እና ከሌሎች ህዝቦችና አገሮች ጋር ግንኙነቶችን ሲያደርግ የቆየ መንግስት/ሱልጣኔት ነበር፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታት የራሱ ስርዋ መንግስትና የራሱ ወደብ የነበረው ሀዲያ በወረራና በጦርነት የተነሳ በብዙ የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ ሌላ ብሄር ሆነዉ የቀሩና በትልቅ ብሔሮች የተዋጡ ቢሆንም አሁን የሀዲያ ዞን ተብሎ በሚጠራበት ቦታ ብቻ እንኳን ብዛታቸዉ እስከ 5 ሚሊዮን የሚገመት የህዝብ ብዛት አለዉ። (በሀገርቱ ያለው አጠቃላይ ከሀዲያ ሱልጣኔት የፈለቁ ብሄሮች ሕዝብ ብዛት አንድ ላይ ቢቆጠር ከ30 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል)።

በተደጋጋሚ በደረሰበት የወረራ ጦርነቶች የተነሳ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ሱልጣኔቱ ከፈረሰ በኋለም ቢሆን በጎሳና በብሔር ገራዶች (በሀገር በቀል ዴሞክራሲ በችሎተቸዉ ብቻ በህዝብ በተመረጡ መሪዎቹ) ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ በ1890ዎቹ የምኒሊክ ጦር የሀዲያን ምድር ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሀዲያ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣኑን ያጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የሀዲያ ፖለቲካ ችግር ምንጩ ሀዲያን ለ130 አመታት ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መገለልና መድሎዎ የዳረገው በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ምስረታ ወቅት ሀዲያ ቀድሞ በእጁ የነበረውን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ተነጥቆ በአንድ ማንነት፣ አንድ ባህል፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት መሰረት ላይ በቆመች አግላይ የአብሲኒያ ኢምፓየር ቁጥጥር ስር መውደቁ ነው። የሀዲያ ህዝብም የተነጠቀውን መብቶቹን ለመመለስ በተለያዩ ጊዜዎች ጦርነቶችና ሰላማዊ ትግሎችን አድርጓል።የሀዲያ ብሔር ራስ ገዝነትን ባጣባቸዉ ዘመናትም ቢሆን ለእኩልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣኑን ለመስመለስ ከመታገል የተቆጠበበት ዘመን አይገኝም። ለዚህም ማሳያ የሚሆን ወደ ሩቅ ቀደምት ታሪክ ዉስጥ ሳንገባ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ገዥውን ፓርቲ ኢህአዴግን በሁለት ተከታታይ ምርጫዎች በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሸነፈና ለዚህም አያሌ ልጆቹን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለእስር፣ ለእንግልትና ለስደት የገበረ ኩሩ ሕዝብ ነው። የሀዲያ ብሔር ማንነትና ራስ ገዝነት በታሪክ የተረጋገጠ እና ቀጣይነት ያለው መሆኑን ታሪክን ወደ ኋላ ዞር ብሎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡

• በመካከለኛው ከፍለ ዘመን (ከ5ኛ እስከ 15ኛ ክፍለ ዘመን) በክብረ ነገስት መዋዕል እንደሰፈረው የአክሱም ንጉስ የነበረው ምኒልክን ጨምሮ የሰሜናዊው የኢትዮጵያ ነገስታት ከሀዲያ መንግስት ጋር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን ያካሄዱ እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ንባብ የተወሰደውም የሰሜናዊው የኢትዮጵያ ነገስታት ስለ ሀዲያ መንግስት ጥንካሬ የሰጡት የምስክርነት ቃል ነው፡፡

• የአረብ የታሪክ ምሁር አል-ኡመር እንደጸፈው የሀዲያ ስርወ መንግሥት በአስራ አራተኛው ምዕተ-ዓመት አጋማሽ የዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ጉዞን የሚፈጅ (ሪቻርድ ፓንክርስት ከ160 -180 ኪ.ሜ ርዝማኔ እንደሚሆን ገልጿል) ሰፊ ግዛት ነበረው፡፡

• ከ13ኛ እስከ 15ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የሀዲያ ሱልጣኔት (ስርወ መንግስት) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኝ የዜይላ ወደብ ፌዴሬሽን አባል የነበረ ጠንካራ ራስ ገዝ አስተዳደር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

• በርካታ የሰሜኑ ኢትዮጵያ መንግሥታት የሀዲያ ሴቶችን በማግባት የጋብቻ ትስስር ይደረግ እንደነበረና የሀዲያ ታላቋ ንግስት እሌኒ የሰሜኑን መንግስት ለረጅም አመታት እንደመራች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

• ሀዲያ እ.ኤ.አ. በ1520ዎቹ ከደቡባዊ ምእራብ ሸዋ አንስቶ ደቡባዊ ምስራቅ የዝዋይና የላንጋኖ ሃይቆች አካባቢን ጨምሮ በስተ ደቡብ ከከምባታ፣ ጋሞ እና ዋጅ ጋር የሚዋሰን ሰፊ ግዛት እንደነበረው ፖርቱጋላዊው የታሪክ ጸሃፊ አልቫሬዝ ጽፎታል፡፡

• እ.ኤ.አ. በ1850ዎቹ የሀድያ መንግስት ከሐይቆች አከባቢ አንስቶ በስተሰሜን ምዕራብ ከጉራጌ፣ የም (ጃንጀሮ) እና ከከምባታ ጋር የሚዋሰን ሰፊ ግዛት እንደነበረው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

• እስከ እ.ኤ.አ.1890 ድረስ የሀድያ መንግስት የራሱን አስዳደር ጠብቆ መቆየቱን፣ በኢማም ሀሰን ኤንጃሞ የተመራው የሀዲያ ጦር ከምኒልክ ጦር ጋር ለአራት አመታት እልህ አስጨራሽ ጦርነት አካሂዶ በመጨረሻ የዘመናዊ ጦር የበላይነት በነበረው በራስ ጎበና ዳጬ ጦር ተሸንፎ እ.ኤ.አ. ከ1890 ወዲህ ራስ ገዝነቱን አጥቶ በሸዋ ክፍለ ሀገር በከምባታና ሀዲያ አውራጃ ስር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡

• እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም. የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት ዳግም ሊመሰረት ችሏል፡፡

• እ.ኤ.አ. በህዳር ወር 2018 የሀድያ ብሔራዊ ምክር ቤት የሀዲያ ብሔራዊ ክልል እንዲመሰረት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የሀዲያ ህዝብ ለዘመናት ሲንከባለል የቆየውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በሰላማዊ፣ ዲሞክረሲያዊና ሕጋዊ መንገድ ለማስመለስ ሀዲያ በክልልነት እንዲደራጅ ፅኑ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል። የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በህዳር ወር 2011ዓ/ም በተደረገ ስብሰባ በጥያቄው ላይ ተወያይቶ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት የሀዲያ ብሔራዊ ክልል እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ ወሰኗል፡፡ ውሳኔውንም ለደቡብ ክልል ምክር ቤት የላከ ቢሆንም በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 47 (3/ለ) መሰረት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጥያቄው ከቀረበበት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ማደራጀት ባለመቻሉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ አቅርቧል፡፡ 

ነገር ግን የፌዴራል መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት ለተጠየቀ ግልጽ ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በቅድሚያ የሚፈልገዉን ዉጤት የወሰነ ባለ80 አባላት ያሉት     ኮሚቴ አደራጅቶ ወደየ ዞኖቹ ልኮ “ሕዝብ” አወያይቷል፡፡ ባለ80 አባላት የያዘ ኮሚቴ ራሱ በኮሮና ወራርሽኝ ምክንያት ስራውን አቁሞ በቤት በተቀመጠበት ወቅት የኮሚቴ አባላት እንኳን በማያውቁት መንገድ፣ ከመጀመሪያው በኮሚቴ አባልነት ባልተካተቱት በእነ አቶ አባዱላ ገመደ  አማካይነት ጥያቄ ያቀረቡ ብሔሮችን መብት የሚደፈጥጥ የክላስተር ክልል አወቃቀር እንደ ውሳኔ ሀሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አቅርቧል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የሀዲያ ክልልነት ጥያቄውን በማፈን ሀዲያ፣ ከምባታ፣ ሀላባ፣ ስልጤ፣ ጉራጌና የም የተካተቱበት ሌላ ትንሽ የደቡብ ክልል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ይህ አካሄድ የሀዲያን ህዝብ መብት የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር የህግ የበላይነትን የሚጻረር፤ በህግና በመንግስት ላይ አመኔታ የሚያሳጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሚያደርግ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የሀዲያ ዳያስፖራ አባላት የሚከተለውን ባለ4 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

  1. የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት ሀዲያ በክልልነት እንድደራጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ያቀረበውን ህገ መንግስታዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰራት ብቻ ሕዝባ ውሳኔ እንዲያደራጅ አጥብቀን እንጠይቀለን፣
  2. የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ሀዲያን ከከምባታ፣ ሀላባ፣ ስልጤ፣ ጉራጌና የም ጋር በማጣመር ሊመሰርት ያቀረበው የክላስተር ፖለቲካዊ አደረጃጀት ኢ-ህገ መንግስታዊ,ና ተቀባይነት የሌለው፣ ህዝቦችን ለአላስፈላጊ ግጭትና ተያያዥ ችግሮች የሚዳርግ መሆኑን አጥብቀን እናስገነዝባለን፣
  3. የፌዴራል መንግስት በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የሀዲያ ብሔርን ሉዐላዊነትና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በመጣስ በሰላማዊ የሀዲያ ህዝብ ላይ የሚያደረሰውን ወታደራዊ አፈናና ኢ-ሰብኣዊ ድርግቶች እንዲያቆምና የልዩ ሃይል ወታደሮችን ከሀዲያ ክልል በአስቸኳይ እንዲያወጣ አጥብቀን እንጠይለን፤ 
  4. ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ያላችሁ የኢትዮጲ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከጎናችን እንዲትቆሙና ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄያችንን ይዘን ለመብታችን በጋራ እንድንታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን፣

የክልል ጥያቄ መልስ ከላይ ወደታች የሚላክ ሳይሆን ከታች ወደ ላይ በህዝበ ዉሳኔ ነው፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

88 thoughts on “በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በኢሲያና በሌሎችም የአለም ዙሪያ ከሚገኙ የሀዲያ ተወላጆች የተሰጠ የአቋም መግለጫ”

%d bloggers like this: