Hadiya Flag on Wide Leaf Background

ኢ-ህገ መንግስታዊ ትናንሽ የደቡብ ክልሎች የፈራሹ ደቡብ ክልል ችግሮች ሁሉ ያሉባቸዉ እንደሚሆኑ እርግጠኞች ነን። ይህን መካድ ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ ይጣፍጣል እንደማለት ነዉ።

ስለ ሀዲያ ክልልነት ጥያቄ ወቅታዊ ሁኔታ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የሀዲያ ተወላጆች የተሰጠ ወቅታዊ የአቋም መግለጫ

የሀዲያ ዞን ምክር ቤት የሀዲያን ክልል ለማቋቋም በሙሉ ድምጽ የወሰነበት ታሪካዊ ውሳኔ እነሆ አራተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።

ሰሞኑን የሀዲያ ብሔር ሽማግሌዎች የጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የማስታወሻ ሀውልት በበህላዊ ምረቃ ሥነስርዓት በከፈቱበት አጋጣሚ ሀዲያ ራሱን ችሎ በክልል ለመደራጀት ያቀረበዉ ጥያቄ ባለመመለሱ ቅሬታቸዉን በመግለጽ ሀዲያ ይህ ተፈጥሮአዊና ህገ መንግስታዊ  መብቱ እንድከበርለት ጠይቀዋል። ጥያቄው በረጅም ደማቅ ጭብጨባና ጩሀት የታጀበ ነበር። ለሀዲያ አባቶች ያለንን ክብርና አድናቆት በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን።

በአጭሩ ሽማግሌዎቹ ያስቀመጡት ሀዲያ እንደ እኩል ብሔር የሚፈለገዉ ለአገራዊ መስዋዕትነት ሲሆን ብቻ መሆኑንና በተቀረዉ የአገር ባለቤትነት የሌለዉ የሁለተኛ ደረጃ ዜጋ መሆኖኑን ህዝቡ ለዘመናት ጠንቅቆ የተረዳዉ ጉዳይ መሆኑን ነዉ። ሀዲያ ከሃያ ዓመታት በላይ መንግሥት የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን በምርኮ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም መልስ ሳያገኝ ቆይቷል። ምንም ዓይነት የምርኮኞች ልዉዉጥ ሙከራ አልተደረገም። የሃገር ባለዉለታ የሆነው ጀግናችን ሞቶም ከሆነ አፅሙ እንኳን እንዲመጣ የተረገ ጥረት የለም። የማስታወሻ ሀውልት እንኳን ለጀግናዉ ልጁ ህዝብ ከኪሱ ከፍሎ ነዉ ያሰራለት። የክልልነት ጥያቄዉ ችላ መባሉ ያዉ አንዱ ማሳያ ነዉ። ችላ መባሉ ሳያንስ ጥያቄዉን ጠንከር አድርገዉ የጠየቁ የሀዲያ ልጆች ለእስርና ለእግልት ነዉ የተዳረጉት።

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የሀዲያ ክልልነት ጥያቄውን በማፈን ሌሎች ትናንሽ የደቡብ ክልሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ቆይተዋል፡፡ ይህ አካሄድ የሀዲያን ህዝብ መብት የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር የህግ የበላይነትን የሚጻረር፤ በህግና በመንግስት ላይ አመኔታ የሚያሳጣና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሚያደርግ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የሀዲያ ዳያስፖራ አባላት ጥቂት የአቋም መግለጫዎችን ማውጣችን ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የሀዲያ ብሄር ህገ መንግስታዊ መብቱን ተነጥቆ ቀጥሏል፡፡

የሀዲያን እና አገራዊዉን ወቅታዊ ሁኔታ በማጤን አሁንም የሚከተለውን ባለ5 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

  1. ትናንሽ የደቡብ ክልሎችን ለመፍጠር የሚደረገዉን ማንኛዉንም ማታለያ እናወግዛለን፡፡ የክላስተር ፖለቲካዊ አደረጃጀት ኢ-ህገ መንግስታዊና ተቀባይነት የሌለው፣ ህዝቦችን ለአላስፈላጊ ግጭትና ተያያዥ ችግሮች የሚዳርግ መሆኑን አጥብቀን እናስገነዝባለን፡፡ ትናንሽ የደቡብ ክልሎች የፈራሹ ደቡብ ክልል ችግሮች ሁሉ ያሉባቸዉ እንደሚሆኑ እርግጠኞች ነን። ይህን መካድ ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ ይጣፍጣል እንደማለት ነዉ። ነገር ግን ትናንሽ የደቡብ ክልሎች ተጨማሪ ችግሮችን ይዘዉ እንሚመጡም አንጠራጠርም፣ 
  2. ሀዲያን ጨምሮ በኢትዮጵ ያሉ ብሄር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ በእኩልነት እንድታዩና የሃገር ባለቤትነታችዉ በተግር እንድረጋግጥላቸዉ እንጠይቃለን፣
  3. ለሀዲያ መብት በሰላማዊ መንገድ ጠንከር አድርገዉ የጠየቁ የሀዲያ ልጆች ለእስርና ለእግልት መዳረጋቸዉን እጅግ አድርገን እንቃወማለን።
  4. የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት ሀዲያ በክልልነት እንድደራጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ያቀረበውን ህገ መንግስታዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰራት ብቻ በሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ አጥብቀን እንጠይቀለን፣
  5. በህብረ ብሄራዊ ፌዴራል አወቃቀር በአንድነት በመኖር የምታምኑ ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ያላችሁ የኢትዮጲ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከጎናችን እንዲትቆሙና ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄያችንን ይዘን ለመብታችን በጋራ እንድንታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን፣

የክልል ጥያቄ መልስ ከላይ ወደታች የሚላክ ሳይሆን ከታች ወደ ላይ በህዝበ ዉሳኔ (referendum) ብቻ ነው፡፡

አጭር አባሪ ጽሁፍ ስሀዲያ ብሔር ታሪክ፣ ራስ ገዝነት ለሀዲያ አዲስ አይደለም

የሀዲያ ብሔር በመካከለኛው ኢትዮጵያ ጠንካራ የሀዲያ ስርወ መንግስት መስርቶ ለብዙ መቶዎች አመታት ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር የኖረ፣ የራሱ ግዛት የነበረው፣ የዜይላ ወደብ ፌዴሬሽን አባል የነበረና የታወቀ የውጪ ንግድ ግንኙነት የነበረው፣ በማንነቱ፣ በባህሉና በቋንቋው ኩሩ የሆነ ብሔር ነው። ሀዲያ የዳበረ የአስተዳዳር ስርአትና ባህል ያለው እና ከሌሎች ህዝቦችና አገሮች ጋር የንግድ ግንኙነቶችን ሲያደርግ የቆየ መንግስት/ሱልጣኔት ነበር፡፡ ለብዙ መቶ ዓመታት የራሱ ስርዋ መንግስትና የራሱ ወደብ የነበረው ሀዲያ በወረራና በጦርነት የተነሳ በብዙ የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ ሌላ ብሄር ሆነዉ የቀሩና በትልቅ ብሔሮች የተዋጡ ቢሆንም አሁን የሀዲያ ዞን ተብሎ በሚጠራበት ቦታ ብቻ እንኳን ብዛታቸዉ እስከ 5 ሚሊዮን የሚገመት የህዝብ ብዛት አለዉ። (በሀገርቱ ያለው አጠቃላይ ከሀዲያ ሱልጣኔት የፈለቁ ብሄሮች ሕዝብ ብዛት አንድ ላይ ቢቆጠር ከ30 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል)።

በተደጋጋሚ በደረሰበት የወረራ ጦርነቶች የተነሳ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ሱልጣኔቱ ከፈረሰ በኋለም ቢሆን በጎሳና በብሔር ገራዶች (በሀገር በቀል ዴሞክራሲ በችሎተቸዉ ብቻ በህዝብ በተመረጡ መሪዎቹ) ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ በ1890ዎቹ የምኒሊክ ጦር የሀዲያን ምድር ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሀዲያ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣኑን ያጣበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

የሀዲያ ፖለቲካ ችግር ምንጩ ሀዲያን ለ132 አመታት ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መገለልና መድሎዎ የዳረገው በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ምስረታ ወቅት ሀዲያ ቀድሞ በእጁ የነበረውን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ተነጥቆ በአንድ ማንነት፣ አንድ ባህል፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት መሰረት ላይ በቆመች አግላይ የአብሲኒያ ኢምፓየር ቁጥጥር ስር መውደቁ ነው። የሀዲያ ህዝብም የተነጠቀውን መብቶቹን ለመመለስ በተለያዩ ጊዜዎች ጦርነቶችና ሰላማዊ ትግሎችን አድርጓል።የሀዲያ ብሔር ራስ ገዝነትን ባጣባቸዉ ዘመናትም ቢሆን ለእኩልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣኑን ለመስመለስ ከመታገል የተቆጠበበት ዘመን አይገኝም። ለዚህም ማሳያ የሚሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የገዥ ፓርቲ ኢህአዴግን ለሁለት ተከታታይ ምርጫዎች በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ያሸነፈ፤ በነዚህ ምርጫ ሂደቶች ወቅትም አያሌ ልጆቹን በሞት ያጣ፣ ሌሎችን ለአካል ጉዳት፣ ለእስር፣ ለእንግልትና ለስደት አሳልፎ የሰጠ ኩሩ ሕዝብ ነው። 

ነገር ግን የሀዲያ ብሔር ማንነትና ራስ ገዝነት በታሪክ የተረጋገጠ እና ቀጣይነት ያለው መሆኑን ለመረዳት ትንሽ ወደ ቀደምት ታሪኩ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡

በመካከለኛው ከፍለ ዘመን (ከ5ኛ እስከ 15ኛ ክፍለ ዘመን) በክብረ ነገስት መዋዕል እንደሰፈረው የአክሱም ንጉስ የነበረው ምኒልክን ጨምሮ የሰሜናዊው የኢትዮጵያ ነገስታት ከሀዲያ መንግስት ጋር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን ያካሄዱ እንደነበር ይናገራል፡፡ ይህ ንባብ የተወሰደውም የሰሜናዊው የኢትዮጵያ ነገስታት ስለ ሀዲያ መንግስት ጥንካሬ የሰጡት የምስክርነት ቃል ነው፡፡

የአረብ የታሪክ ምሁር አል-ኡመር እንደጸፈው የሀዲያ ስርወ መንግሥት በአስራ አራተኛው ምዕተ-ዓመት አጋማሽ የዘጠኝ ተከታታይ ቀናት ጉዞን የሚፈጅ (ሪቻርድ ፓንክርስት ከ160 -180 ኪ.ሜ ርዝማኔ እንደሚሆን ገልጿል) ሰፊ ግዛት ነበረው፡፡

ከ13ኛ እስከ 15ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የሀዲያ ሱልጣኔት (ስርወ መንግስት) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኝ የዜይላ ወደብ ፌዴሬሽን አባል የነበረ ጠንካራ ራስ ገዝ አስተዳደር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

ሀዲያ ለዘመናት አልገዛም ባይና ተዋጊ ህዝብ ስለነበረ በርካታ የሰሜኑ ኢትዮጵያ መንግሥታት የሀዲያ ሴቶችን በማግባት የጋብቻ ትስስር ያደርጉ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡  የሀዲያ መሪ ገረድ ልጅ እሌኒ መሀመድ ለአብነት ትጠቀሳለች፡፡ በአቢሲኒያ  ታሪክ ገናና ከሆኑት የሴት ነገስታት አንዷና ታላቋ ንግስት እሌኒ ለረጅም ዓመታት በጋራ አገርን እንደመራች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ንግስት እሌኒ ዘርዓ-ያዕቆብ ባለቤትና ለተከታታይ ነገስታት ባዕደ-ማርያምን፣ እስክንድርን እና ናኦድን በተነገረለት አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ጥበቧ ችግር ፈቺና አማካሪ ሆና እንዳገለገለች ከበርካታ መዛግብት እንረዳለን።

እ.ኤ.አ. በ1316/17 የአቢሲኒያ ወደ ደቡባዊ ግዛቶች የመስፋፋት ዘመቻዎች የመጀመሪያዉ እንደሆነ የሚነገርለት የአጼ አምደ ጽዮን ወረራ በሀዲያና በዳሞት መንግስታትን ላይ ነበር የጀመረዉ። በወቅቱ የሀዲያ ሁሉ አቀፍ ገዢ ገራድ አመኖ ወረራውን የመመከት የጦር ዘመቻ ቢመራም መጨረሻ ላይ ሀዲያ እ.ኤ.አ. በ1332 ገባር ግዛት ተደረገ። በገራዶቹ ስርዓት ራስ ገዝነቱን ግን እንደ አሁን ሙሉ በሙሉ አልተወሰደበትም ነበር።

እ.ኤ.አ. 1434-68 የሀዲያ መሪ ገረድ መሂኮ ወይም መዩኮ (የገረድ መሀመድ ልጅና የንግስት እሌኒ ወንድም) ሀዲያ ለአቢሲኒያ መንግሥት አይገብርም ብሎ አመጸ። ከበርካታ ዉጊያዎች በኋላ የአቢሲኒያ ከፋፍለህ ግዛ ፖለትካ ሀዲያን ስለከፋፈለዉ ፃመጹ ከሽፏል። ገራድ መዮኮ ከወታደሮቹ ጋር ወደ አዳል ኮበለለ። ሆኖም የአጼ ዘረ ያቆብ መንግሥት ከዳሞት ግዛት የቀጠራቸዉን ወታደሮ ወደ አዳል ግዛት በመላክ ገራድ መዮኮን ከመግደሉም በላይ ራሱንና ሰዉነቱን በመቆራረጥ ለአጼዉ ቁርጥራጬን አቅርበዋል።  አጼዉ ታማኝ አገልጋያቸዉን የመዮኮን አጎት ባሞን (ቦያሞ)የሀዲያ ገራድ አድርገዉ ሾሙት።

ሀዲያ እ.ኤ.አ. በ1520ዎቹ ከደቡባዊ ምእራብ ሸዋ አንስቶ ደቡባዊ ምስራቅ የዝዋይና የላንጋኖ ሃይቆች አካባቢን ጨምሮ በስተ ደቡብ ከከምባታ፣ ጋሞ እና ዋጅ ጋር የሚዋሰን ሰፊ ግዛት እንደነበረው ፖርቱጋላዊው የታሪክ ጸሃፊ አልቫሬዝ ጽፎታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1850ዎቹ የሀድያ መንግስት ከሐይቆች አከባቢ አንስቶ በስተሰሜን ምዕራብ ከጉራጌ፣ የም (ጃንጀሮ) እና ከከምባታ ጋር የሚዋሰን ሰፊ ግዛት እንደነበረው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

እስከ እ.ኤ.አ.1875-94 የሀዲያ ጎሰዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ የአጼ ምኒልክን ወረራ የመመከት በርካታ እልህ አስጨራሽ ጦርነቶችን አካሂደዋል።

እስከ እ.ኤ.አ.1890 ድረስ የሀድያ መንግስት የራሱን አስዳደር ጠብቆ መቆየቱን፣ በኢማም ሀሰን ኤንጃሞ የተመራው የሀዲያ ጦር ከምኒልክ ጦር ጋር ለአራት አመታት እልህ አስጨራሽ ጦርነት አካሂዶ በመጨረሻ የዘመናዊ ጦር የበላይነት በነበረው በራስ ጎበና ዳጬ ጦር ተሸንፎ እ.ኤ.አ. ከ1890 ወዲህ ራስ ገዝነቱን አጥቶ በሸዋ ክፍለ ሀገር በከምባታና ሀዲያ አውራጃ ስር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም. የሀዲያ ብሔራዊ ምክር ቤት ዳግም ሊመሰረት ችሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በህዳር ወር 2018 የሀድያ ብሔራዊ ምክር ቤት የሀዲያ ብሔራዊ ክልል እንዲመሰረት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ድል ለጭቁኑ ሕዝብ!

11-FEB-2022

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: